በበጀት አመቱ የደንብ መተላለፎች በ81.3% መቀነስ መቻሉ ተገለፀ ።
በበጀት አመቱ የደንብ መተላለፎች በ81.3% መቀነስ መቻሉ ተገለፀ ።
20/10/2018 ዓ.ም
**አዲስ አበባ**
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱን የባለስልጣኑ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ከክፍለ ከተማና ወረዳ ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ኃላፊዎች ጋር በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫዎች አስቀምጧል ።
በመድረኩ የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት ጠንካራ አፈፃፀሞችን ያስመዘገበ መሆኑን ገልጸው፣ የተገኙ ስኬቶችን ይበልጥ ለማስቀጠልና የታዩ ክፍተቶችን በ2019 በጀት ዓመት ለመሙላት መድረኩ መዘጋጀቱን አስገንዝበዋል።
ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በበጀት ዓመቱ ካከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል በተለይ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በሕግ ማስከበር፣ በተቋም ግንባታ እና በሰው ኃይል አቅም ማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ርቀት መጓዙ ተገልጿል።
ቀደም ሲል አናሎግ የነበረውና በቀን ለ12 ሰዓታት ብቻ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው የ9995 የጥሪ መስመር ወደ ዲጂታል በመቀየር፣ በአሁኑ ወቅት በአምስት ቋንቋዎች የ24 ሰዓት ሙሉ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተገልፆ በቀን ከ200 እስከ 300 የሚደርሱ ጥቆማዎችን በመቀበል፣ ከሕዝብ በሚገኝ መረጃ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የመፈፀም አቅምን ለማሳደግ ለነባር ኦፊሰሮች እና አመራሮች በኢትዮጽያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በሰንዳፋ እና በአዳይቱ የመፈጸም አቅምን የሚያሳድጉ ጠንካራ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል።
በኮሪደር ልማት የተሰሩ መሰረተ ልማቶችን ከመጠበቅ አንፃር ተቋሙ ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል። ከዚህ ባለፈም ከመሬት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ወደ መሬት ባንክ የገቡ መሬቶችን ሙሉ በሙሉ ማስከበር የተቻለ ሲሆን፣ ከ9ኙ የደንብ ጥሰቶች (የጎዳና ንግድ፣ የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ፣ ሕገ-ወጥ ማስታወቂያ እና ሌሎችም) ጋር በተያያዘ በተደረገ ጠንካራ ስራ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ81.3% ብልጫ ያለው ውጤት ተመዝግቧል ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በ2018 በጀት ዓመት በእቅድ አፈጻጸም የተከናወኑ አበይት ተግባራት ፣ የገጠሙ ተግዳሮቶች ፣ የተወሰዱ የመፍትሄ ሪፖርት በባለስልጣኑ እቅድና በጀት ዳይሬክተር ኮለኔል አድማሱ ተክሌ ቀርቧል ።
በመድረኩ የ2019 በጀት ዓመት መሪ እቅድ እና የቀጣይ 90 ቀናት ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።
በመጨረሻም በመድረኩ የተሳተፉ አመራሮችና ዳይሬክተሬቶች በቀረበው ሪፖርት እና እቅድ ላይ ሀሳብናና ጥያቄዎች አቅርበው ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቶበት ቀጣይ የስራ አቅጣጫ ዋና ስራ አስኪያጁ አስቀምጠዋል ።
ዘገባው፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው
።
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments