እውነተኛ የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮች ለማፍራት ጥራት ያለው ይዘት በማዘጋጀት ከተከታዮች ለሚቀርቡ አስተያየቶች ፈጣን ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል" ዶ/ር ደስታ ተስፋው የብልጽግና ፖርቲ ኢንስፔክሽንና ስነምግባር ኮ/ን ዋና ኮሚሽነር
"እውነተኛ የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮች ለማፍራት ጥራት ያለው ይዘት በማዘጋጀት ከተከታዮች ለሚቀርቡ አስተያየቶች ፈጣን ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል" ዶ/ር ደስታ ተስፋው የብልጽግና ፖርቲ ኢንስፔክሽንና ስነምግባር ኮ/ን ዋና ኮሚሽነር
10/07/2018 ዓ.ም
**አዲስ አበባ**
የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ለማዕከል ፣ለክፍለ ከተማ እና ለወረዳ የደንብ ማስከበር ለኮሙዩኒኬሽን ፎካል ፐርሰኖች (የሚዲያ ሰራዊት) በድህረ እውነታ ዘመን (Post-Truth) የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ የግንዛቤ ስልጠና ተሰጠ ።
በመድረኩ የተገኙት የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ የሚዲያ ተጽዕኖ በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች የዲጂታል ክህሎታቸውንና ሥነ-ምግባራቸውን በየጊዜው በማሳደግ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን መከላከልና አወንታዊ ሚናውን ማጠናከር እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
አክለውም የኮሙኒኬሽን ስራዎች ለተቋም ግንባታና የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባራትን ተደራሽ ለማድረግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ የተለያዩ ሚዲያዎችን በመጠቀም የባለስልጣኑን መረጃ በማሰራጨትና ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የደንብ መተላለፍን የሚጸየፍ ለተቋሙ አጋዥ የሚሆን ህብረተሰብ መፍጠር ላይ መሆኑን ገልፀዋል ።
በድህረ እውነታ ዘመን የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ስልጠና የፌደራል የብልጽግና ፖርቲ ኢንስፔክሽንና ስነምግባር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ደስታ ተስፋው ተሰጥቷል ።
ስልጠናው በዋናነት ባለሙያዎች በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የሐሰት መረጃዎችን የመለየትና ተቋማዊ ተልዕኮን ለማሳካት ሚዲያውን በአግባቡ የመጠቀም አቅማቸውን ለማሳደግ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።
በሚዲያው ውጤታማ ተግባቦት እንዲኖር መልእክቶች ግልጽ፣ አጭር፣ የተሟሉና ትክክለኛ መሆን እንዳለባቸው ተመላክቷል።
በተጨማሪም አንድ ጥሩ ኮሙዩኒኬተር ንቁ አድማጭነት፣ ሀሳብን በግልጽ የማቅረብ እና ራስን ከተመልካች ጋር የማስማማት ክህሎቶች ሊኖሩት እንደሚገባ በስልጠናው ተገልጿል።
ባለሙያዎች ስራቸውን ውጤታማ ለማድረግ ግልጽ ግብ መቅረጽ፣ ተከታዮችን መለየት፣ ጥራት ያለው ይዘት ማዘጋጀትና ለሚቀርቡ አስተያየቶች ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው እንዲሁም መረጃዎችን ከመለጠፍ በፊት ከታማኝ ምንጮች ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ዶ/ር ደስታው ገልጸዋል ።
የባለስልጣኑ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ምስራች ግርማ በአሁኑ ወቅት ማህበራዊ ሚዲያ መረጃን ለማድረስ ብቻ ሳይሆን የህዝብን አስተሳሰብ ለመቅረጽና የግንዛቤ ማስጨበጫ ለመስጠት ዋነኛው መሳሪያ በመሆኑ እያንዳንዱ የፎካል ፐርሰን አባል በየደረጃው የሚከናወኑ የደንብ ማስከበር ስራዎችን ለህዝብ ሲያሳውቅ፣ በስልጠናው ያገኘውን ክህሎት በመጠቀም የተዛቡ ትርክቶችን የመመከትና የተቋሙን ገጽታ የመገንባት ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል።
በመጨረሻም በቀረበው ሰነድ ዙሪያ ከተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ውየይት በማድረግ ለተነሱ ሀሳብና ጥያቄዎች ከመድረኩ ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት የተዘጋጀው የፎቶ ኢግዚብሽን እና የተቋም ግንባታ ስራዎች በመጎብኘት ስልጠናው ተጠናቋል ።
ዘገባው:- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ነው
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments