
ባለስልጣኑ መጪው የመስቀል የደመራ እና የእሬቻ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ውይይት አካሄደ
ባለስልጣኑ መጪው የመስቀል የደመራ እና የእሬቻ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ውይይት አካሄደ
10/ዐ1/2018 ዓ.ም
**አዲስ አበባ**
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን መጪው የመስቀል ደመራ እና የእሬቻ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የባለስልጣኑ ከፍተኛ አመራሮች ከክፍለ ከተማ እና ከወረዳ ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ኃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂዷል ።
በመድረኩ የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ መስቀልና ኢሬቻ በዓላት በዓለም የማይዳሰስ ቅርስ የተመዘገቡ የመተሳሰብ፣ የአብሮነት፣የአንድነት በዓላት እንደመሆናቸው ሀይማኖታዊና ባህላዊ እሴትቻቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ ከህብረተሰቡ ጋር እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል ።
አክለውም በዓሉ በሚከበርበት ወቅት በከተማዋ ላይ የተሰሩትን የኮሪደር መሰረተ ልማቶች እንዳይበላሹ ህብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ከደንብ ማስከበር እና ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ከተማችንን ጽዱ እና ውብ እንድትሆን መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል ።
የ2018 የመስቀል ደመራ እና የእሬቻ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ አጭር የማስፈጸሚያ እቅድ በባለስልጣኑ የደንብ መተላለፍ ክትትል ፣ቁጥጥር እና እርምጃ አወሳሰድ ዳይሬክተር አቶ ግሩም ወ/መስቀል ቀርቧል።
በበዓላት ወቅት ሊፈጸሙ የሚችሉ የደንብ መተላለፎችና ተያያዥ ህገወጥ ተግባራት እንዳይኖሩ በዓሉ ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅና በበዓሉን አስመልክቶ አላሰፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖርና የግባእት እጥረት እንዳያጋጥም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መስራት እንደሚያስፈልግ በእቅዱ ተገልጿል ።
በመድረኩ የተገኙት የባለስልጣኑ ም/ስራ አስኪያጅ አቶ ከፍያለው ታደሰ በዓሉን አስመልክቶ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የፀጥታችግሮችና ሌሎች የደንብ መተላለፎች እንዳይከሰቱ ከወዲሁ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግና በዓልን ምክንያት በማድረግ የሚፈጸሙ የደንብ ጥሰቶችን ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ተግባርን ማከናወን እንደሚገባ ገልጸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በዓላቱ ከደንብ ጥሰት በጸዳ እና ያለምንም የፀጥታ ችግር ይከበሩ ዘንድ የሚጠበቅብንን ሚና እንወጣለን ሲሉ ገልፀዋል።
በመጨረሻም ከተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ ለተነሱ ሀሳቦችና ጥያቄዎች ከመድረኩ ምላሽና አስተያየት ተሰጥቶበት መድረኩ ተጠናቋል ።
መረጃው ፡-የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳሬክቶሬት ነው፡፡
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments