
የአራዳ ክ/ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት አዲስ ሰልጥነው ወደ ክፍለ ከተማው ለተመደቡ የፓራ-ሚሊታሪ ኦፊሰሮች አቀባበል አደረገ
የአራዳ ክ/ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት አዲስ ሰልጥነው ወደ ክፍለ ከተማው ለተመደቡ የፓራ-ሚሊታሪ ኦፊሰሮች አቀባበል አደረገ
ሰኔ 12/ 2017 ዓ.ም
****በአዲስ አበባ****
በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በ6ኛ ዙር የፓራ-ሚሊታሪ ስልጠናቸውን አጠናቀው አራዳ ክ/ከተማ ለተመደቡ 294 የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች የፌዴራልና አዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ አዛዦች እንዲሁም የከተማ፣ ክ/ከተማና የወረዳ አመራሮች በተገኙበት አቀባበል ተደረገ።
የአራዳ ክ/ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌታሁን አበራ እንደተናገሩት ተባባሪና ቀና የሆነውን የአራዳን ህዝብ ማገልገል ክብር ነው ብለው ከተማዋ ያለችበትን ፈጣን የልማት እንቅስቃሴ የሚመጥን የህግ መተላለፍና የደንብ ጥሰቶችን መከላከል የሚያስችል ቀጣይነት ያለው የተቀናጀ ስራ ያስፈልጋል ብለዋል።
የልማት ስራችንን የበለጠ ለማጠናከር በ3 ፈረቃ ለሚሰራው የደንብ ማስከበር ስራ ውጤታማነት በሁሉም ወረዳዎች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የገለጹት አቶ ጌታሁን የመንግስት አላማ ህግን የሚያከብር ትውልድ መፍጠር በመሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጥና ደንብ የማስከበር ስራውን ጎን ለጎን ማስኬድ ከእያንዳንዱ ኦፊሰር የሚጠበቅ መሆኑን አሳስበዋል።
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የአራዳ ክ/ከተማ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ተወዳጅ ኃ/ማርያም መንግስት የበለጸገች ሀገርን ለመገንባት የሚያደርገው ጥረት ግቡን ሊመታ የሚችለው ህግ ሲከበርና የደንብ ጥሰት እንዳይኖር ማድረግ ሲቻል መሆኑን ገልጸው በ6 ዙር ስልጠና ወስዳችሁ አራዳ ክ/ከተማ ላይ የተመደባችሁ የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች መንግስት አምኖ የሰጣችሁን ሀላፊነት በአግባቡ እንድትወጡ ሲሉ አደራ ብለዋል።
በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው ተቋሙ የደንብ ማስከበር ስራውን ለማዘመንና ውጤታማ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልጸው 7/24 የሚያገለግሉ አመራሮችን አርአያ በመከተል ህዝቡን በትህትና እንድታገለግሉ ሲሉ አዲስ ወደስራ የገቡትን ኦፊሰሮች አሳስበዋል።
ተቋሙ የሚፈልገው ንቁና ብቁ የሰው ሀይል በመሆኑ የሀገሪቷ ዋና ዋና ተቋማት መገኛ የሆነችዉን የአራዳ ክ/ከተማን ሰላምና ጸጥታ ማስከበርና የደንብ ጥሰት እንዳይከሰት የማድረግ ስራው በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት የአራዳ የአራዳ ክ/ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አብዲ ሙሉነህ በሰለጠናችሁት መሰረት ከነባር ኦፊሰሮችና ሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅታችሁ በፍጹም ትጋት ህዝባችሁን እንድታገለግሉ ሲሉ አደራ ብለዋል።
በዛሬው እለት የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል መርሀ ግብር የተዘጋጀላቸው 294 ኦፊሰሮች ግንቦት 30/2017 ተመርቀው ሰኔ 1/2017 ስራ መጀመራቸውን የገለጹት የአራዳ ክ/ከተማ ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ሀላፊ ሻምበል ኑርልኝ ገ/ኪዳን የደንብ ማስከበር ስራውን በማጠናከር የወንጀል መንስኤዎችንና የንግድ አሻጥሮችን ለመከላከል ከህዝቡና ባለድርሻ የጸጥታ አካላት ጋር በጥምረት በ3 ፈረቃ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በመጨረሻም የደንብ ጥሰትና የወንጀል ድርጊቶችን ቀድሞ ለመከላከልና ተከስተው ሲገኙ የእርምት እርምጃ በመውሰድ የከተማዋን ሰላም በማስቀጠል ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ ሁሉም ነዋሪ ከጸጥታ አካላቱ ጎን ሆኖ መስራት እንደሚገባው ተገልጿል።
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments